የሔኖክ ታሪክ ለልጆች \ The story of Enoch for children \የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ለሕፃናት
Вставка
- Опубліковано 9 лют 2025
- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የተዋሕዶ ፍሬዎች፣ የሃገር ተስፋዎች እንደምን ሰነበታችኁ ልጆች? “እግዚአብሔር ይመስገን ደኅና ነን" አላችችኁ? መልካም።
፩፪፫፬፭፮፯፰፱፲
ዛሬ ስለአንድ አስገራሚ ፃድቅ ሰው እነግራችዃለኹ ፣
የምነግራችኹ ድንቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ፣ ስሙ ቅዱስ ሄኖክ ስለሚባል እና አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ እና እግዚአብሔርን ስላስደሰተ ወደ ሰማያተ ሰማይ መንግስተ ሰማያት እግዚአብሔርን ይዞት ስለሄደ ፃድቅ ሰው እነግራችዃለኹ ፣
ልብ ብላችኹ አዳምጡኝ እሺ ፣ ጎበዞች ።
ጥንተ ጠላታችን - ዲያብሎስ ሰዎችን ሁሉ ከእግዚአብሔር ማራቅ እችላለሁ ብሎ ኹሌም ይከራከራል። ይህ ክርክሩ የሰመረለት የተሳካለት የመሰለባቸው ወቅቶች ነበሩ።
ቀደም ሲል በነገርኳችኹ ታሪክ የአዳም ልጅ አቤል ወንድሙ ቃየን ገድሎት ከሞተ በኋላ ለብዙ ዓመታት ለማለት ይቻላል አንድም ሰው የታመነ የእግዚአብሔር አገልጋይ ለመኾን አልበቃም ነበር ፣ ከዚህ ይልቅ ኃጢአትና ክፋት በምድር ላይ ነግሦ ነበር።
ሄኖክ የተወለደው አምላክ ምድርን ከፈጠረ ብዙም ሳይቆይ ነው። እንዲያውም ሄኖክ ሲወለድ የመጀመሪያው ሰው የኹላችን አባት አዳም በሕይወት ይኖር ነበር።
ሄኖክ ወደ ምድራችን ብቅ ያለው መንፈሳዊነት ባዘቀጠበት እግዚአብሔርን መፍራት ለእግዚአብሔር መታዘዝ በተተወበት በዚህ ወቅት ላይ ነበር ። ሄኖክ በወቅቱ ከነበረው ትውልድ በተለየ መልኩ የአምላክን ሞገስ አግኝቶ ነበር።
ሄኖክ በጣም ልዩ ሰው ነበር ፣ ሄኖክ እግዚአብሔርን ስለሚፈራ እና ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ለእግዚአብሔር ልዩ ነበር ።
ሄኖክ ለእግዚአብሔር አክብሮት በሌላቸው ሰዎች መካከል ቢኖርም ‘አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አድርጓል።
አያት ቅድመ አያቶቹ የነበሩት የአዳም የልጅ ልጆች ሴት፣ ሄኖስ፣ ቃይናን፣ መላልኤልና ያሬድ አካሄዳቸውን ከአምላክ ጋር አደረጉ አልተባለላቸውም። ቢያንስ ቢያንስ በአኗኗር መንገዱ ከእነርሱ እንደተለየው እንደ ሄኖክ አላደረጉም።
ሄኖክ ወደ እግዚአብሔር የቀረበ ነበር ፣ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ እና እግዚአብሔርም በጣም ወደደው። ምክንያቱም ሄኖክ የእግዚአብሔር ወዳጅ እና አጋር ነበር።
‘ሄኖክ አካሄዱን ከእውነተኛው አምላክ ጋር አደርጓል’ ፣ ‘ሄኖክ አምላክን አስደስቶታል’ ፣ ሄኖክም የእግዚአብሔር ወዳጅ በመሆኑ ብቻ ተደስቶ ይኖር ነበር ።
እግዚአብሔር በሰማይ ሳለ ሄኖክ በምድር ቢኖርም ይኽ ግን ሄኖክን ወደ እግዚአብሔር ከመቅረብ አላገደውም።
ምንም እንኳን በውስጡ እግዚአብሔርን በእጁ መንካት ባይችልም ወይም እግዚአብሄርን በምድር ዓይኖቹ ማየት ባይችልም ከእግዚአብሄር ፍቃድ ጋር መሄዱን አላቋረጠም።
በልቡም በአእምሮውም በመንፈሱም ወደ እግዚአብሔር የቀረበ ፃድቅ ሰው ነበር።
ሄኖክ በማለዳ ከእንቅልፉ ሲነቃ ዛሬ ሊያደርግ የሚፈልገውን አስደሳች ነገር አያስብም ይልቁንስ እግዚአብሔር የሚፈልገውን እግዚአብሔርን ሊያስደስት ይችላል የሚለውን ተግባር እነ ስነ ምግባር ብቻ ያስብ ነበር።
ከእግዚአብሔርም ጋር ኹሌ ይነጋገር ነበር ፣ እግዚአብሔር ሆይ ዛሬ ስለኛ ስለ-ፍጥረታት ምን እያሰብክ ነው? ዛሬ ምን ባደርግ ያስደስትሃል? እያለ ከልቡ እግዚአብሔርን ይጠይቅ ነበር።
ሄኖክ በቀን ውስጥ በከተማው ውስጥ ሲዘዋወር ፣ " ያ ሰው ጥሩ ቤት አለው" ወይም " ያ ሰው ብዙ አስደሳች ነገሮች አሉት" "እንደዚህ አይነት ነገሮች ቢኖሩኝ እመኛለሁ" እያለ አላሰበም ፣
ይልቁንም "በምድር ዓይኖቼ የማያቸው እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለትንሽ ጊዜ ወይም ጊዜያዊ ብቻ ናቸው። እግዚአብሔር አንተ ግን የማትታይ ነህ። አንተን ከማየት ውጪ ሌላ ምንም የሚያስደስት ነገር የለም ። እግዚአብሔር ሆይ በጣም እወድሃለሁ ፣ ስለ አንተ ሁሉንም ነገር እወዳለሁ። ይል ነበር ሄኖክ።
ሄኖክ በውሎው ኹሉ ቀኑን ሙሉ ስለ ተከሰተው ነገር ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር ሕይወቱን እንዲህ ኖሯልና ፣ የእግዚአብሔርም ፍቃድ ኾኖ ሄኖክ እግዚአብሔርን ጠንቅቆ ማወቅ ጀመረ።
ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አድርጓል መባሉ ከመለኮታዊ ፈቃድ ጋር ተስማምቶ በመኖሩ ምክንያት ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጋር መቀራረቡን እንዲሁም ወዳጅነት መፍጠሩን የሚያሳይ ነው።
ሄኖክና እግዚአብሔርም በዚኽ መልኩ ሲቀራረቡ፣ ሲቀራረቡ እግዚአብሔርም ሄኖክ ማየት ከሚችለው በላይ እንዲያይ ፈቅዶ ለወጠው።
ልጆችዬ የሚገርማችኹ ሄኖክ የሚታየውን ብቻ ሳይሆን የማይታየውንም ዓለም ማየት ጀመረ።
በፊቱ ሙሉ በሙሉ የተለየ ዓለም ማለትም የማይታይ ዓለም እንዳለ ማየት ችሏል። የእግዚአብሔር ፍቃድ ከሌለ ሰዎች ይህንን የማይታየውን ስውር ዓለም ማየት አይችሉም።
ሄኖክ ግን በሰማይ አይኖች ስላየ ይኽንን ድብቅ ዓለም በእግዚአብሔር ፍቃድ መላእክት እያዘዋወሩ አስጎብኝተውታል ሰው ያላየውን ለማየት ችሏል ።
ሄኖክ በየቀኑ ሲመላለስ እና ከእግዚአብሔር ጋር ሲነገር፣ ሄኖክ እና እግዚአብሔር እውነተኛ ጓደኞች ሆኑ።
ሄኖክ ማቱሳላንም ከወለደ በኋላ 300 ዓመት ኖረ ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ. ሄኖክ በአጠቃላይ 365 ዓመት ኖረ።
ልጆች " እድሜህን የማቱሳላ ያድርግልኽ" ብለው ትልልቅ ሰዎች ምርቃት ሲመርቁ ሰምታችኹ ታውቃላችኹ?
ማቱሳላ የሄኖክ ልጅ ነው ፣ በምድር ላይ እንደሱ ረዥም እድሜ የኖረ ቀድሞም አልነበረም እስከዛሬም የለም ማቱሳላ በምድራችን ላይ 969 ዓመት ኖሯል ፣
ወደ ርዕሳችን የሄኖክ ታሪክ ስንመለስ ፣
ሄኖክ ከእግዚአብሔር ጋር በታማኝነት እድሜውን ሙሉ ተጉዟል ፣ እግዚአብሔርም ወደሰማየ ሰማያት ስለ ወሰደው አልተገኘም።
ይኽ እንዴት ሊኾን እንደቻለ ታውቃላችኹ ልጆች?
ቀጥዬ የምነግራችኹን ልብ ብላችኹ አዳምጡ ፣
እግዚአብሔር እና ሄኖክ ዘወትር አብረው ይነጋገሩ ነበር። ኹልጊዜ ሄኖክ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገርና እግዚአብሔርን ሲያደስት ቆይቶ ፣
ከእለታት አንድ ቀን እግዚአብሔር ሄኖክን እንዲኽ አለው ፣
ወደዚህ እንድትመጣ እና በገነት ከእኔ ጋር እንድትሆን በእውነት እፈልጋለሁ
ልጆችዬ ሄኖክ የእግዚአብሔርን ድምጽ እንደወደደው ትጠራጠራላችኹ?
በፍጹም!
ከዛ በኋላም ሄኖክ ከሰው ዓይን ጠፋ ፣ ከሰው ልጆች ሁሉ ሞትን ያልቀመሰ ከጥቂቶቹ አንዱ ኾኖ ወደ መንግሥተ ሰማያትም ተወሰደ ፣ እግዚአብሔር ሄኖክን በጣም ስለወደደው ከእርሱ ጋር ይኖር ዘንድ ወደ መንግስተ ሰማያት ወሰደው።
እግዚአብሔር እንዳለ ፣ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንደሚሰጥ የሰው ልጅ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋልና ፣ ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም ፣ ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና ።
ሄኖክ በዛ በመንግስተ ሰማያት አሁን ደስተኛ ፣ እጅግ ደስተኛ ፣ ደስተኛ ኾኖ እየኖረ ነው ፣ በሰማይም ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም ይኖራል።
ከሄኖክ ምን እንማራለን❓
ሄኖክ የኖረበት ዓለም ልክ እንደኛ ዓለም ሁሉ ዓመፀኛ፣ ስሙን የሚያረክስና ፈሪሃ አምላክ የሌለው ነበር። ሆኖም ሄኖክ በዚያን ጊዜ የነበረውን ዓለም አካሄድ አልተከተለም። እውነተኛ እምነት የነበረውና ለእግዚአብሔር አምላክ ያደረ በመሆን ለሌሎች ምሳሌ ነበር ስለዚኽም እግዚአብሔር አምላክ ሄኖክን ሞት እንዳያገኘው ጥበቃ አድርጎለት ወደ መንግስተ ሰማያት ወስዶታል።
የተወደዳችኹ የተዋህዶ ልጆች የኢትዮጵያ ሃገራችን እንቁዎች ልክ እንደ ሄኖክ የእግዚአብሔር ወዳጅ መሆን ትፈልጋላችኹ ፣ አይደል❓ ጎበዞች ።
እንግዲያውስ እንዲኽ አድርጉ
👉 ከእግዚአብሔር ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር
በመጀመሪያ ደረጃ እሱ ስለሚወደውና ስለሚጠላው ነገር ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ያስፈልጋል ፣ ስለ ሃይማኖታችኹ ተማሩ ጠይቁ እወቁ።
ቤተክርስቲያን በምታዛችኹ እድሜያችኹ በሚፈቅደው መልካም ተግባር ኹሉ በመሳተፍ ፣ በሰንበት ትምህርት በመሳተፍ ፣ በአገልግሎት ፣ በጾም ፣ በጸሎት ፣ በስግደት ፣ በመዝሙር
አዎን፣ አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር ለማድረግ እሱን ማስደሰት ይኖርብናል
እንዲኹም መምህራን የሚሏችኹን በመስማት ፣ እናት አባታችኹን ፣ ወንድም እኽቶቻችኹን ፣ ጎረቤት ወዳጅ ዘመድ ሰውን ኹሉ ይልቁንም ታላላቆቻችኹን በማክበር እና በመውደድ
ልክ እንደ ሄኖክ አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር ለማድረግ እሱን ማስደሰት ይኖርብናል ፣
👉 እምነት አካሄዳችንን ከአምላክ ጋር እንድናደርግና ልቡን ደስ የሚያሰኝ ጠባይ እንድናሳይም ይገባል፣ይኽ ሲኾን የእግዚአብሔር ወዳጅ መሆን ትችላላችኹ።
👉 ጻድቁ ሄኖክ እምነቱ አምላካዊ ፍርሃት ባልነበረው ዓለም ውስጥ አካሄዱን ከአምላክ ጋር አድርጎ እንዲሳካለት እንደረዳው ሁሉ እኛም ሊሳካልን ይችላል።
ልጆችዬ ሌሎች አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉ ቅዱሳን እና ፃድቅ ሰዎች አስገራሚ ድንቃድንቅ ታሪክ በተከታታይ ይዤላችኹ እመጣለኹ ፣
እስከዛው ደኽና ኹኑ ልጆች
ወስብሃት ለእግዚአብሔር
Betammmm gobez egziyaber yistln
እግ/ር ይመስገን
❤❤❤❤❤😊😊😊😊❤️🧡💛💚💙💜🖤💔❣️
የሔኖክ ልጆች ስንት ናቸዉ