የኦሮሞ ታሪክ/History of Oromo ቦረና እና ባሬንቱ

Поділитися
Вставка
  • Опубліковано 5 лют 2025
  • የኦሮሞ ማኅበረሰብ ታሪክ
    የኦሮሞ ማኅበረሰብ በቋንቋ ምሁራን ዘንድ ኩሻዊ ተብሎ የሚጠራ ምድብ ውስጥ የሚመደብ ቋንቋን የሚናገር ብሔረሰብ ሲሆን የሚገኘውም በኢትዮጵያ እና በሰሜን ኬንያ ነው። በስነ ሰብዕ አጥኚው በኸርበርት ኤስ. ሉዊስ ገለፃ የኦሮሞ እና የሶማሌ ማኅበረሰቦች የተነሱት በደቡብ ኢትዮጵያ ሲሆን ሶማሌዎች ወደ ሰሜን እና ወደ ምስራቅ ቀደም ብለው ተስፋፉ፤ ኦሮሞ ግን በ1522 ዓ.ም ገደማ እስካደረጋቸው መስፋፋቶች ድረስ በአሁኗ ኢትዮጵያ ደቡባዊ ክፍል እና በአሁኗ ኬንያ ሰሜናዊ ክፍል ብቻ ይኖር ነበር። የብሔረሰቡ ተወላጅ እና የታሪክ አጥኚ የሆኑት መሐመድ ሀሰን 'The Oromo and the Christian Kingdom of Ethiopia: 1300-1700' በሚለው መጽሐፋቸው በገለጹት መሰረት 'ኦሮሞ' የሚለው ቃል የመጣው 'ኢልም ኦርማ' ከሚል ቃል ሲሆን ትርጉሙም የኦርማ ልጆች ማለት ነው። በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ኦርማ የኦሮሞ ሁሉ አባት እንደሆነ ይታመናል።
    የኦሮሞ ህዝብ በታሪክ መዝገብ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የተጠቀሰው በ1452 ዓ.ም ተሰርቶ በተጠናቀቀው እና የካርታ ሰሪው የፍራ ማውሮ ስራ በሆነው በታዋቂው ማፖሞንዶ ወይም የዓለም ካርታ ላይ ነበር፤ በዚህም መሰረት ከአዋሽ ወንዝ በደቡብ የሚገኝ የኦሮሞ ወንዝ አለ። ይህም የኦሮሞ ህዝብ ወደ ሰሜን ከመስፋፋቱ በፊት ቢያንስ አንድ ክፍለ ዘመን ከግማሽ ለሚሆን ጊዜ ያህል ይህን አካባቢ ይዞ ለመኖሩ ማሳያ ነው። ገና ከ12ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የኦሮሞ ህዝብ ሙሉ ሕይወቱ በገዳ ሥርዓት የተቃኘ ነበር፤ ይህ የገዳ ሥርዓት ዕድሜን መሰረት ያደረገ መንግሥታዊ እና መንፈሳዊ ሥርዓት ነው። በገዳ ሥርዓት ውስጥ በየ ስምንት ዓመቱ ኦሮሞ ዘጠኝ አመራሮችን ይሾማል፤ እነዚህ አመራሮችም ሳልጋን ያይ ቦረና ይባላሉ፤ ትርጉሙም ዘጠኙ የቦረና ስብስቦች ማለት ነው። በገዳ ሥርዓት የተመረጠ መሪ በሥልጣን መቆየት የሚችለው ለ8 ዓመታት ብቻ ነው፤ 8ቱ ዓመታት ከተጠናቀቁ በኋላ በቦታው ሌላ ሰው ይመረጣል። አንድ አባ ገዳ ተግባራቸውን በሚከውኑባቸው ዓመታት መካከል ቢሞቱ ቦኩ(ሥልጣናቸውን የሚወክለው በትር) ለሚስታቸው ይተላለፋል፤ እርሷም ቦኩውን(ሥልጣን የሚወክለውን በትር) ይዛ ህግጋትን ትደነግጋለች።
    ስለ ኦሮሞ ማኅበረሰብ ሰፋ ያለ የታሪክ መረጃ ለመጀመርያ ጊዜ የፃፉት ኢትዮጵያዊው መነኩሴ አባ ባህሬይ ናቸው። በፕሮፌሰር ማእምር መናእሰማይ ጥናታዊ ጽሑፍ መሰረት አባ ባህሬይ በደቡብ በሚገኘው በጋሞ ምድር ይኖሩ የነበሩ ኦርቶዶክስ መነኩሴ ናቸው። በአባ ባህሬይ ገለፃም የኦሮሞ ህዝብ የአርብቶ አደር ህዝብ ሲሆን በሁለት ቡድኖች የተከፈለ ነው፤ እነዚህም በረይቱማ እና ቦረን ናቸው። እነዚህ ሁለቱም መስፋፋት የጀመሩት የከብቶቻቸው ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ ስለነበር የግጦሽ መሬት እያነሳቸው ስለነበር ነው። በየ ስምንት ዓመታቱ በሚቀያየሩ ሉባ የተባለ ማዕረግ ባላቸው አመራሮች ስርም ሆነው ከቦረና ተነሱ፤ አባቶቻቸው ያልያዙትንም መሬት እየያዙ ሄዱ። የኦሮሞ የቦረን ጎሳ የሆኑት ዳዌ እና ጃዊ አባ ባህሬይ የነበሩበትን ምድር ጋሞን ባጠቁ ጊዜ ያላቸውን ንብረት ሁሉ እንደወሰዱባቸው ገልጸዋል።
    አባ ባህሬይ በኦሮሞ ላይ ግልፅ ቂም ቢኖርባቸውም ኃይለኛ ተዋጊ መሆናቸውን ግን አልካዱም። እንደገለጹትም ከሆነ በኢትዮጵያ ክርስትያኖች ላይ የበላይነት የሰጣቸው ነገር አለ። ይህም የኢትዮጵያ ክርስትያኖች መነኩሴ፣ ቄስ፣ ዳኛ፣ ሽማግሌ፣ ባለሙያ፣ አንጥረኛ እና ወዘተ ተብለው የተለያየ የስራ ክፍል ስለሚይዙ የወታደሮች ቁጥር ትንሽ ነው፤ በኦሮሞ ዘንድ ግን ሁሉም ወንድ ከትንሽ እስከ ትልቅ በጦር ሜዳ ይሰለፋል ብለው ያብራሩታል።
    በፕሮፌሰር ሪቻርድ ፖንክኸርስት ገለፃም መሰረት አባ ባህሬይ ሁለት ነገሮችን ከግምት ውስጥ አላስገቡም፤ እነዚህም አንደኛ የክርስትያኗ ግዛት እና የሙስሊሟ የአዳል ግዛት በኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም አል-ጋዚ በተከፈቱት ዘመቻዎች ምክንያት አውዳሚ ጦርነቶች ውስጥ እንደገቡ፤ ሁለተኛ ደግሞ ኦሮሞ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሚገኙ ህዝቦችን የመጠቅለል ችሎታ እንዳለው ከግምት ውስጥ አላስገቡም።
    ኦሮሞ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ከማድረጉ በፊት በሁለት ሕብረት የተከፈለ ነበር፤ እነዚህም ቦረና እና ባሬንቱ ናቸው፤ ቦረና በስምጥ ሸለቆው በምዕራብ፣ ባሬንቱ በስምጥ ሸለቆው በምስራቅ ይገኙ ነበር። ባሬንቱ ወደ አሁኖቹ አርሲ፣ ባሌ እና ሀረርጌ ሲገፋ፤ ቦረና ደግሞ ወደ ሸዋ፣ ኢሉባቡር እና ወለጋ ገፋ።
    በእነዚህ መግፋቶችም ብዙ ፈረሶችን ማረኩ፤ የገዳ ሥርዓቱም የኦሮሞ ፈረሰኛዎችን በማቀናጀት ውጤታማ በሆነ ሁኔታ እንዲዋጉ አደረጋቸው። ኦሮሞ ደዋሮን ሲወር የተመለከተው ፖርቹጋላዊው የዜና መዋዕል ጸሐፊ ጃዎ ቤርሙደስ የኦሮሞን የውትድርና ሥነ ሥርዓት እንዲህ ብሎ ገልጾታል፦ "የመጡት እንደ ኋላ ቀሮች ያለ ሥርዓት አልነበረም፤ ነገር ግን እንደ ቡድን ተደራጅተው በአንድነት ነበር"
    በሉባዎች በሚመራው በገዳ ሥርዓትም በኦሮሞ የተያዙ ብሔረሰቦች 'ገበሮ' እና 'ሞጋሳ' በተባሉ ሥርዓቶች አማካኝነት ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን እና ጠቅላላ ማንነታቸውን ወደ ኦሮሞ ይቀይራሉ።
    በብሔረሰቡ ተወላጅ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት እንዲሁም የሳዮ ኦሮሞ ላይ ጥናት ያደረጉት ነጋሶ ጊዳዳ በጦርነት እና በሞጋሳ ሥርዓት ከ20 በላይ ብሔረሰቦች ወደ ኦሮሞ ማንነት ተጠቅልለዋል። ከእነዚህም ውስጥ ጋፋት፣ ማያ፣ አንፊሎ እና ወርጂ ይገኙበታል። ዛይ፣ አርጎባ፣ ሀረሪ እና ሺናሻ ህዝብንም አዳክሟል።
    በአህመድ ዘካሪያ ገለፃም ኦሮሞ ወደ ሐረርጌ በመጣ ጊዜ ከኢሚር ኑር ኢብን ሙጃሂድ ጦር ጋር ገጥሞ አሸነፈ። ኢሚር ኑርም ሀረርን በጀጎል ግንብ ያጥር ዘንድ ግድ ሆነበት፤ ይህ ግንብም የሀረር ህዝብ ማንነትን ያስጠበቀ ግንብ ነው። ኋላም የአዳል ሱልጣኔት ተዳክሞ በወደቀ ጊዜ ኢማም መሐመድ ጋሳ ዋና ከተማውን ከሀረር ወደ አውሳ አዘዋወረ። በተመሳሳይ ጊዜም የክርስትያን ሰሎሞናዊያን ንጉሠ ነገሥታትም መቀመጫ በሸዋ ካሉት ከደብረ ብርሃን እና ቴጉላት ወደ በጌምድር ጎንደር ተዘዋወረ።
    በ16ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ኦሮሞ ከአባይ ወንዝ በደቡብ በአሁኗ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከደረሰ በኋላ ከከፋ ጋር ገጥሞ ከፋን ከጎጀብ ወንዝ ተሻግሮ እንዲሄድ በመግፋት በ60 ዓመታት ውስጥ አምስት የጊቤ ግዛቶችን መሰረተ። እነዚህም ጌራ፣ ጎማ፣ ጉማ፣ ጅማ እና ሊሙ-ኢናርያ ናቸው። በኦሮሞ ትውፊትም የከፋ ህዝብ ጅማን እንዲለቅ ያደረገችው ንግሥት ማክሆሬ ትባላለች። ሊሙ-ኢናርያም የተመሰረተው የኢናርያ ንጉሣዊ ቤተሰብ ሂናሬ ቡሻሾ ጎሳ ተገልብጦ ነው። በዚህም አካባቢ ያለ ኦሮሞ ከአርብቶ አደርነት ወደ አርሶ አደርነት ተለወጠ፤ የዚህም ምክንያቱ አካባቢው ለምለም እና ብዙ ውኃ ያለው መሆኑ ነው። ይህ የግብርና አስፈላጊነት መጨመርም የመሬት ይዞታ ያላቸው ሰዎች ኃያልነትን ጨመረ። ይህ ባለጠጋ መሬትም ብዙ ፈላጊ ያላቸው ውጤቶችን እንዲይዙ አደረጋቸው፤ ይህም ብዙ ነጋዴዎች እንዲኖሩ አደረገ። እነዚህ ለውጦችም የገዳ አስተዳዳሪዎች የተሻለ ሥልጣን እንዲተገብሩ እና በየ ስምንት ዓመቱ የሚቀየሩበትን ሥርዓት ወደ ንጉሣዊ ሥርዓት እንዲቀይሩ አስቻላቸው። በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል በአርሲ፣ በባሌ እና በሀረርጌ የሚገኙት ኦሮሞዎች እስከ 19ነኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ በስፋት አርብቶ አደር ሆነው ዘለቁ። በምስራቅ ካሉት ውስጥ ግብርናን እንደ ዋና ሥራ የያዙት ለሀረር ከተማ በቅርበት የነበሩት ኦሮሞዎች ብቻ ነበሩ፤ እነርሱም ያንን የሚያደርጉት ከታጠረችው ከተማ ነዋሪዎች ጋር ለመገበያየት ነበር። በቃል እና በጽሑፍ ማስረጃዎች መሰረት በ16ተኛው፣ በ17ተኛው እና በ18ተኛው መቶ ክፍለ ዘመናት አንዳንድ የሶማሌ እና የኦሮሞ ጎሳዎች በተለይ ለምስራቅ ድንበር ቅርብ በሆኑ ቦታዎች እርስ በእርስ ይዋጉ ነበር።
    ማጣቀሻዎች(References)
    1. en.wikipedia.o...
    2. books.google.c...
    3. en.wikipedia.o...
    4. www.universal-...
    5. አጤ ምኒልክ - በጳውሎስ ኞኞ: dirzon.com/Doc...
    6. journals.ju.ed...
    7. en.wikipedia.o...

КОМЕНТАРІ • 76