የላስታ ታሪክ/History of Lasta የላሊበላ ታሪክ
Вставка
- Опубліковано 5 лют 2025
- በ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በ960 ዓ.ም የመጨረሻው የአክሱም ንጉሥ አፄ ድል ናዖድ በሰሜን ንጉሥ በጌድዮን አራተኛ ሴት ልጅ በቤተ እስራኤላይቱ ዮዲት ጉዲት ከተሸነፈ በኋላ አክሱምን ሸሽቶ ሄደ፤ በዚህም የአክሱም መንግስት አከተመ። ዮዲትም ከ960 ዓ.ም እስከ 1000 ዓ.ም ለ40 ዓመታት መርታ ከሞተች በኋላም አገሪቱ ውስጥ የሥልጣን መበታተን እና ብጥብጥ ሆነ። በዚህም ጊዜ አንድ መራ ተክለ ሐይማኖት የተባለ ሰው በትረ መንግሥቱን ጨብጦ መናገሻ ከተማውን ወደ ላስታ በማዞር የዛግዌ ሥርወ መንግስትን መሰረተ። ዛግዌ የሚለዉ ስያሜ የሥርወ-መንግሥቱ አባላት የነገደ አገው ተወላጆች ስለኾኑ የአገው መንግሥት ለማለት ’’ዘአገው’’ ከሚለው የግዕዝ ቃል የወሰዱት ነው፡፡
ከመራ ተክለሃይማኖት ጀምሮ ዐሥራ አንድ ተከታትለው የመጡ የዛግዌ ነገሥታት ማዕከላቸውን በላስታ አድርገው አገሪቱን እንደ አስተዳደሩ ትውፊታዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከነዚህም መካከል አራቱ ክህነትን ከንግሥና ጋር አስተባብረው የያዙ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ በቅድስናቸዉ የሚታወቁ ናቸው፡፡ እነዚህም ነገሥታት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን ዘንድ፦ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ሐርቤ(ገብረ ማርያም)፣ ቅዱስ ላሊበላ እና ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ከ11ዱ ተከታታይ የዛግዌ ነገሥታት እነዚህ አራቱ የዛግዌ ነገሥታት ለክርስትና እምነት የተለየ ፍቅር ይኑራቸው እንጂ፤ ሁሉም የዛግዌ ነገሥታት ክርስቲያኖች ስለነበሩ በዮዲት ጉዲት የጥፋት ዘመቻ ምክንያት ተመናምኖ የነበረውን ክርስትና እንደገና እንዲያንሠራራ፣ ተስፋ የቆረጠዉን ሕዝበ-ክርስቲያን እንዲፅናና፣ የተቃጠሉ መጽሐፍት እንደገና እንዲፃፉ እንዲሁም የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናት እንደገና እንዲሰሩ ያደረጉት ጥረት፤ በኢትዮጲያ ቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የሚረሳ አይደለም፡፡ ከሁሉም በበለጠ አራቱ ነገሥታት ሙሉ ሕይወታቸውን ለመንፈሳዊ ነገር አዉለዉ አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽ የክርስትና ሐይማኖት እንዲከበር፣ እንዲስፋፋና እንዲጠናከር በማድረግ ቤተክርስቲያንን ያገለግሉ ስለሆኑ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅድስና ማዕረግ ሰጥታቸዋለች፡፡
የመጀመርያው የዛግዌ ንጉሥ እና የሥርወ መንግስቱ መስራች መራ ተክለ ሐይማኖት የተወለደው በላስታ ነበር፤ በዛም ማዕከሉን አደረገ። መራ ተክለ ሐይማኖትም ከላስታ አልፎ ዋግን፣ ትግራይን እና ሰሜን በጌምድርን በእርሱ አስተዳደር ውስጥ አስገባቸው። ንጉሥ መራ ተክለ ሐይማኖትም የመጨረሻውን የአክሱም ንጉሥ የአፄ ድል ናዖድን ሴት ልጅ መሶበ ወርቅን አገባት፤ ከእርሷም ታታዲም፣ ጃን ስዩም እና ግርማ ስዩም ተወለዱለት። በነገሥታት ዝርዝርም መሰረት መራ ተክለ ሐይማኖት ለ13 ዓመታት በንግሥና ከቆየ በኋላ ሞተ፤ በቦታውም ዜና ጴጥሮስ ነገሠ።
በዘመኑም ዜና ጴጥሮስ የዳሞት ግዛትን ሊስገብር ፈለገ፤ ነገር ግን የዳሞት ሰዎች ለእርሱ ለመገበር ፈቃደኛ አልነበሩም፤ በዚህም ዜና ጴጥሮስ ከላስታ ተነስቶ በዳሞት ላይ ዘመቻ ከፈተ፤ ነገር ግን የዳሞት ሰዎች ከላስታ የመጣውን የዛግዌ ሠራዊት በጦርነት አሸነፉት፤ በዚህም ዜና ጴጥሮስ ዳሞትን ያስገብር ዘንድ አልቻለም። በዘመኑ የዳሞት ግዛት ሰዎች ደስክ የተባለ የራሳቸውን አምላክ የሚያመልኩ የራሳቸው ሐይማኖት የነበራቸው ስለሆኑ ከክርስትያኗ የዛግዌ ግዛትም ሆነ ከሙስሊሟ የሸዋ ሱልጣኔት ጋር ስምምነት አልነበራቸውም። የክርስትያን እና የሙስሊም ግዛቶችንም እየወረሩ አገራቸውን ያስፋፉ ነበር፤ ከዚህም በላይ ዳሞት በአንድ ወቅት የሸዋ ሱልጣኔትን በጉልበት ግብር ያስከፍል ነበር።
በ1013 ዓ.ም ዜና ጴጥሮስ ከተገደለ በኋላ ታታዲም በላስታ ላይ በትረ መንግስቱን ጨብጦ የዛግዌ ንጉሥ ሆነ። የታሪክ አጥኚው ታደሰ ታምራት እንደገለጸው ከሆነ ታታዲም የዛግዌ ሥርወ መንግስት መስራች የመራ ተክለ ሐይማኖት የመጀመርያ ልጅ ነበር። በገድለ ይምሐረነ ክርስቶስ መሰረት ታታዲም እርሱን ተክተው ልጆቹ ንግሥናውን እንዲረከቡ ለማመቻቸት በወንድሞቹ በጃን ስዩም እና በግርማ ስዩም ላይ እርምጃዎችን ሲወስድ ነበር፤ የአገው የውርስ ህግ ግን ወንድሞቹ ተተኪዎቹ እንዲሆኑ ይደነግጋል። ይህም በዛግዌ ነገሥታት ዘንድ ችግር የፈጠረ ነበር። ምክንያቱም ነገሥታቱ ልጆቻቸው እንዲተኳቸው ይፈልጋሉ፤ የውርስ ህጉ ግን ለወንድም ያደላል።
ታታዲምም በሞተ ጊዜም ወንድሙ ጃን ስዩም በላስታ የዛግዌ ሥርወ መንግስት ንጉሥ ሆኖ ተነሳ። የታሪክ ምሁሩ ታደሰ ታምራት እንደዘገበውም ጃን ስዩም የማራ ተክለ ሐይማኖት ልጅ፣ የንጉሥ ታታዲም ታናሽ ወንድም እና የይምሐረነ ክርስቶስ አባት ነበር። ነገር ግን በረጅሙ የነግሥታት ዝርዝር ላይ ስሙ አይገኝም።
ከጃን ስዩም በኋላም ግርማ ስዩም በላስታ የዛግዌ ንጉሥ ሆነ። በአንዳንድ የነገሥታት ዝርዝር ላይም በእምነት በሚባል ስም ተጠቅሷል። ታደሰ ታምራት እንደጠቀሰውም ከሆነ ጃን ስዩም የመራ ተክለ ሐይማኖት ልጅ፣ የንጉሥ ታታዲም ታናሽ ወንድም፣ እና የፐንተወደም፣ የቅዱስ ሐርቤ እንዲሁም የገብረ መስቀል ላሊበላ አባት ነበር።
በጃን ስዩም ቤትም የምታገለግል ኪዮርና የተባለች አንዲት ገረድ ነበረች። ጃን ስዩምም ከእርሷ ጋር ባደረገው ግንኙነት ምክንያት ኪዮርና ከእርሱ ጸንሳ ነበር፤ ጃን ስዩምም ይህንን በሰማ ጊዜ እጅግ ተበሳጨ። ኪዮርናም ሮሃ ወይም አደፋ ወደተባለ በዛው በላስታ ወደሚገኝ ቦታ ለመሸሽ ወሰነች፤ ወደዛም ሸሽታ ልጇን በዚያ ወለደች፤ ህፃኑም በተወለደ ጊዜ ንቦች ከብበውት ነበር፤ እናቱም ይህንን ተመልክታ ላሊበላ ብላ ጠራችው፤ በጥንቱ አገውኛ ላሊበላ ማለት ንቦች ሳይቀሩ ለንጉሥነቱ እውቅና ሰጡ ማለት ነው። ጃን ስዩም ከሞተ በኋላ የጃን ስዩም ታላቅ ወንድም የታታዲም ልጅ ይምሐረነ ክርስቶስ ነገሠ፤ ይምሐረነ ክርስቶስ ከሞተም በኋላ የጃን ስዩም ሌላ ልጅ የላሊበላ ወንድም ቅዱስ ሐርቤ ነገሠ። ቅዱስ ሐርቤም ወንድሙ ላሊበላ በሥልጣኑ እንዳይመጣበት ስለሰጋ በወንድሙ በላሊበላ ላይ በጠላትነት ተነሳበት። በዚህም ወቅት ላሊበላ በመስቀለኛዎቹ ክርስትያኖች ቁጥጥር ውስጥ ወደነበረችው ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት አንድም በጠላትነት ከተነሳበት ወንድሙ ለመሸሽ፤ በሌላም በኩል ደግሞ መንፈሳዊ ጉዞ ለመከወን ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ለዓመታት ተቀመጠና ዳግም ወደ ላስታ ተመለሰ፤ ወደ ላስታም ከተመለሰ በኋላ መስቀል ክብራ የተባለችን ሴት አገባ። ነገር ግን ቅዱስ ሀርቤ አሁንም ንጉሥ ነበረና ዳግም ሊገድለው ተነሳ፤ ላሊበላም ከሚስቱ ጋር ላስታን ለቅቆ መሄድ ግድ ሆነበት።
በመጨረሻም ላሊበላ ዙፋን ላይ ወጣ፤ ነገር ግን እንዴት ወደ ዙፋን እንደወጣ መረጃው የለም። በወንድሙ ዘመን ላይም ወደ ዙፋን በመውጣቱ ምክንያት ታደሰ ታምራት ላሊበላ አክሊሉን የተቀዳጀው በጦርነት እንደሆነ ይገምታል።
ማጣቀሻዎች(References)
1. የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ ክፍል-2 ገጽ 43
2. eprints.soas.a...
3. G.W.B. Huntingford, The historical geography of Ethiopia from the first century AD to 1704, (Oxford University Press: 1989), p. 100
4. Budge, E. A. Wallis (1928). A History of Ethiopia: Nubia and Abyssinia (Volume 1). London: Methuen & Co. p. 285.
5. G.W.B. Huntingford, "'The Wealth of Kings' and the End of the Zāguē Dynasty", Bulletin of the School of Oriental and African Studies, 28 (1965), p. 8
6. www.sacred-dest...
7. whc.unesco.org...
8. www.dirzon.com...